
አዳም ረታ
አዳም ረታ ከ 1970ዎቹ ጀምሮ አጫጭር ልብ ወለዶችን፣ ግጥሞችና የረዥም ልብ ወለድ ድርሰቶች መፃፍ የጀመረ ሲሆን በ1977 በታተመው 'አባ ደፋርና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች' መፅሀፍ ውስጥ አራት ድርሰቶችን አቅርቧል።
የደራሲው የመጀመርያ ወጥ መፅሀፍ የሆነው 'ማሕሌት" በ 1981 ታትሟል። በአጠቃላይ፤ አዳም ረታ ስድስት የአጫጭር ልብ ወለድና አራት የረዥም ልብ ወለድ መፃሕፍትን አሳትሟል።
'ጭጋግና ጠል'፣ 'አማሌሌ'፣ 'መልክዓ ስብሐት' እና 'Addis Ababa Noir' የተባሉ መድበሎች ውስጥም ትረካዎችና ሂሳዊ ዳሰሳዎችን አቅርቧል።
(የመፃሕፍቱን ዝርዝር እዚህ ይመልከቱ)
አዳም ረታ ለ25 አመታት ያህል በሙከራ ላይ የሚገኝ "ሕፅናዊነት" የተባለ የአፃፃፍ ስልት(ፍልስፍና) ይከተላል። ስለ 'ሕፅናዊነት' ተጨማሪ ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ
'እኔ ማሕሌትን ስጽፍ፤ ስለ ሕግ አላውቅም፡፡ ፕሎት፣ ጭብጥ የእንግሊዘኞቹን (ሕጎች) ሁሉ አላውቃቸውም፡፡ የሰራሁት በስሜት ነው፡፡ ታሪከ እንዲህ መሆን አለበት በሚል ነው የተነሳሁት፡፡ እዚያ ውስጥ ሕግ ይዞ ላጥና ለሚል ሕግ ይዤ የተከተልኩባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚያን ግን text book ወስጄ አላነበብኳቸውም፡፡ ከዚህ ስሜት በመነሳት ሌላም ትልቅ ስራ ሕግ ሳትከተል በመስራት ሕጉ የሚጠይቃቸውን አንዳንድ ነገሮች ልታሟላ ትችላለህ፡፡ ሕጉን የሚጻረሩ ነገሮችም ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር ድርሰቱ ሙሉ ነው ወይ? የሚያነበውን ሰው ያዝናናዋል ወይ? የሆነ ነገር ከዚያ ያገኛል ወይ? ያ ነው መፈተሻው፡፡"
ትምሕርት/ የግል ሕይወት
አዳም ረታ የ ጂኦግራፊ ቅድመ ምረቃ ትምርህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በኔዘርላንድስ ተከታትሏል።
በአሁኑ ጊዜ በካናዳ፣ ኦታዋ ይኖራል።
"ጂኦግራፊ ስትማር ስለ መልክዓ ምድር ውበት አትማርም፡፡ Aesthetics የለውም፤ ሳይንስ ነው፡፡ ትመዝናለህ፣ የአለትን ይዘት፣ የተራራን ከፍታ በጫማ (feet) ትለካለህ፡፡ድርሰቴ ውስጥ የተራራን ከፍታ በሜትር የጻፍኩበት ቦታ የለም፡፡ ያደግኩበት አካባቢ የከተማዋ መጨረሻ ነበር፡፡ መልክዓ ምድሩ በጣም የሚያምር ነበር፡፡ አሁን ቤት ተሰርቶበት መንገድ ወጥቶበት ጠፍቷል፡፡ እና ከዚያ መልክዓ ምድር ተምሬያለሁ፡፡ ስለዚህ የማደርገው ነገር፤ ያንን ያደግኩበትን መረጃ መጥራትና መረጃዎቹን ወደየድርሰቶቼ መበታተን ነው፡፡ ይሄ ከጂኦግራፊ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡››