የአዳም ረታ “ሕጽናዊነት” ምንድን ነው?
- ዮሃንስ ገለታ
- Apr 11, 2021
- 17 min read
Updated: Jul 5, 2021
መግቢያ
ከጥቂት ጊዜያት በፊት ፌስቡክላይ በሚገኝ የአዳም ረታ አድናቂዎች ቡድን ውስጥ አንድ ሰነድ አገኘሁ፡፡ ይሄ ከሀያ ገፆች በላይ ያለው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ አዳም በተለያየ ጊዜ በአንባቢዎቹ ለተጠየቃቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጠበት መድበል ነው፡፡ ፋይሉን አንብቤ እንደጨረስኩ ይሄንን ጽሑፍ ማግኘት ላልቻሉ ሰዎች ባጋራ ማንንም እንደማይጎዳ ስላመንኩበት ነው ይሄንን ጽሑፍ ማዘጋጀቴ፡፡ ዋናው ዓላማዬ ግን ሕጽናዊነት ምንድን ነው የሚለውን ትልቅ ጥያቄ በአጭሩ ለመመለስ ያደረግሁት ደፋር ሙከራ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ የአዳምን ጽሑፍ በረጃጅሙ ወስጃለሁ፡፡ አዳም በመጻሕፍቱ ውስጥ ካስቀመጠልን ማብራሪያዎች ላይም ቀነጫጭቤያለሁ፡፡ በአጭሩ ለጋዜጣ ፅሑፍነት እንዲስማማ ማመቻቸት ስለ ነበረብኝ አንዳንድ ቦታ ላይ ብቻ ማያያዣ የሚሆኑ አረፍተ ነገሮችን፤ አንቀፆችንና ምሳሌዎችን ከማስቀመጤ በስተቀር ቀሪው የራሱ የአዳም ቃል ነው፡፡
አዳም እና እንጀራ
እንጀራ ለአዳም የጽሑፉን ቅርፅ የሚቀዳበት ሞዴል ብቻ አይደለም፡፡ “It is more than a model. It is a metaphor” ይላል በራሱ ቃል፡፡ “ከሞዴልነት በላይ ነው፡፡ እንጀራ ተለዋጭ ዘይቤ ነው፡፡
እንጀራ ክብ ነው፡፡ ባለ ሦስት ዲሜንሽን ነው፤ ግን ደግሞ ጠፍጣፋ፡፡ ቀዳዳዎች አሉት ግን ደግሞ ልሙጥ ነው፡፡ በጠጣር እና ጠጣር ባልሆነ ቁስ መካከል የሚገኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የእንጀራው ቀዳዳዎች (ዐይኖቹ ማለቴ ነው) ራሳቸውን ችለው የቆሙ ይመስላሉ፤ ሆኖም ውስጥ ውስጡን ውስብስብና ረቂቅ በሆኑ ቱቦዎች የተያያዙ ናቸው፡፡ በተቃርኖዎች የተሞላ መዋቅር ኖሮትም እንኳ እነኚሁ ተቃርኖዎቹ ‘ቀጥ ብሎ እንዲቆም’ የሚያስችሉት አላባውያኑ ሆነው ይሠራሉ” (It has a contrasting structure signified by opposites and yet all contributing to its whole physical ‘survival’). ሕይወት ራሷ ከተቃርኖዎች ውህድ የተገመደች ነች፡፡ በዚህም እንጀራ ከሕይወት/ህልውና ጋር የተቆራኘ መሆኑን ለመጠቆም አዳም የምሳሌያዊ ንግግሮቻችንን እንደ ማስረጃ ያነሳል፡፡ እንጀራውን ጋገረ፤ እንጀራ ፈላጊ፤ የእንጀራ ገመዱ ተበጠሰ፤ እንጀራ በሬው፤ እንጀራውን ያበስላል ወዘተ፡፡ ህላዌ ቅጥ አልባና የተሰደረ ሁለቱንም ነው፤ ወይም የተሰደረ ቅጥ አልባነት፡፡ (Ordered chaos እንደማለት) አንዱ ከአንዱ የተያያዘ… እንጀራ ይህንን የህላዌን ተቃርኗዊ ግንኙነቶች የሚገልፅ ምሳሌ ነው፡፡ እኔም ይሄንን ዘይቤ ወደ አጻጻፍ ስልትነት ብለጥጠው ብዙም ከዕውነታው አልራራቅም፡፡ “Existence is both chaotic and ordered; or ordered chaos. Interconnected……Injera is used as a metaphor for describing or illustrating existence. And it is not far from the truth if I stretch this metaphor into a writing technique” ይላል አዳም፡፡ እንጀራዊ/ እንጆሪያዊ ቅርፅ ከሕጽናዊነት በፊት እንጀራዊ/እንጆሪያዊ ቅርፅ ነበር፡፡ ሆኖም የቃላት መለዋወጥ እንጂ ጠለቅ ያለ የትርጉም ልዩነት አይታይም፡፡ ምናልባት እንጀራዊ ቅርፅ የሕጽናዊነት እርሾ ወይም ሕጽናዊነት የእንጀራዊ/እንጆሪያዊ ቅርፅ እጅግ የተጠና፤ የላቀና ምልዑ በኩልዔ የሆነ ‘ቨርሽኑ’ ነው፡፡ በ”ግራጫ ቃጭሎች” መግቢያ ላይ እንጆሪያዊ ቅርፅ እንዲህ ተብራርቷል፡ “የዚህን መጽሐፍ የአጻጻፍ ቅርፁን የተዋስኩት ከእንጀራ ቅርፅ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ምዕራፎች ከእንጆሪው ጠቃጠቆ/ንዑስ ፍሬዎች ጋር ወይም ከእንጀራው ዐይኖች ጋር እንዲማሰሉ ሆኖ ነው የቀረበው (አንድ ዐይን ወይም ጠቃጠቆ አንድ ምዕራፍ) … ታዲያ በአሰያየም ውሰት ከእንጆሪ ወደ እንጀራ ከመጣን ለምን ከእንጀራ ወደ እንጆሪ አንሄድም? ከዚያ ወደዚህ የወሰደን መንገድ አይመልሰንም ማን አለ? ወደ መነሻው ሄድኩና ለዚህ ልብ ወለድ ቅርፅ እንጆሪ የተሰኘ ስያሜ ሰጠሁት ወይም መረጥኩ”፡፡ የእንጆሪ ቅርፅ ለሕጽናዊነት እንደ ጥንስስ ቢሆንም ስሙን ይዞ መቆየት አይችልም (“የእንጀራ ቅርፅ” ካልተባለ በስተቀር)፡፡ አዳም “መረቅ” የተሰኘው መጽሐፉ በሃገር ፍቅር ቴያትር ቤት ሲመረቅ፣ ከታዳሚያኑ መካከል በአንደኛው በቀረበለት አስተያየት መሠረት፤ እንጆሪ የሚለውን ቃል ምንም ዓይነት የቲዮሪ መፋለስ ስለማያስከትል ማውጣት እንደሚቻል ተናግሯል፡፡ (ይህ አስተያየት ሰጪ እንዳለው የእንጀራ ዓይኖች (ሰው ሠራሽ በመሆናቸው) አንዱ ከሌላው ያለው ርቀት ዘፈቃዳዊ ነው፤ የእንጆሪው ጠቃጠቆዎች ግን (ተፈጥሯዊ በመሆኑ) በስሌት ሊቀመጥ የሚችል ቅጥ አላቸው)፡፡ ከእንጀራ/እንጆሪያዊነት ወደ ሕጽናዊነት አዳም ከእንጀራ/እንጆሪያዊ ቅርጽ ወደ ሕጽናዊነት ለመሸጋገር ወደ ትናንት ርቆ ይጓዛል፤ በንባቡና በማሰላሰሉ፡፡ “የድሮ ሰዎች እንደኛ ርቱእ (literal) አይደሉም፡፡ ከፊደል ገበታቸው እስከሚበሉት ነገር ብታይ የሆነ ዓይነት ለመፈታት የሚጠብቅ ሚስጥር አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ግንዛቤ ላይ ለመድረስ በሆነ ዓይነት ስነ-ውበታዊ ልምድ (aesthetic experience በሚባለው) ውስጥ አለፍኩኝ፤ ከዚያ ጊዜ በኋላ የዚያን ጠፍጣፋ ዳቦ ትርጓሜ ሳሰላስል ቆይቻለሁ”፡፡ የእንጀራን ዘፍጥረት ፀሐይ ትመለክበት ከነበረው ዘመን እንደሚነሳ ይናገራል አዳም፡፡ “እንጀራ የሚገርም ቅርፅ አለው፡፡ ዘፍጥረቱም ፀሐይ ትመለክበት ከነበረው ዘመን ይነሳል፡፡ በዚያን ዘመን ፀሐይ በክብ ምልክት ትወከል ነበር፡፡ የኛ ፊደል ፀሐዩ ‘ፀ’ የፀሐይ ወኪል ነው፡፡ ዐይኑ ‘ዐ’ም የተባለው ፀሐይ በሰማዩ ላይ ያለች ‘ዐይን’ በመሆኗ ነበር፡፡ የእንጀራን ጉድጓዶች ‘ዐይን’ ማለታችን ገጠመኝ አይመስለኝም”፡፡ “ክብ ከጥንት ጀምሮ የሕብረት፣ የአንድነትና የዘላለማዊነት ምሳሌ ነው፡፡ መካከሉ ላይ አንድ ነጥብ ያለው ሰርከምፓንክ የሚባል ክብ ደግሞ አለ፡፡ ፀሐይን እና የፀሐይ አምላክ (ግብፅ ውስጥ “ራ” የሚባለውን) ይወክላል፡፡ (“እንጀራ” ውስጥ ያለችው “ራ” ከዚህ ጋር ግንኙነት ቢኖራትስ?) ክቡ እና ነጥቧ የወንዴና ሴቴ ኃይሎች መንፈሳዊ ውሕደት ትዕምርት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አለም አቀፋዊ ትርጓሜ ነው” (This is a universal/cosmic sensibility)፡፡ ታዲያስ እንጀራ ስላለፈው ዘመን እንዲዘክር በዕቅድ የተወጠነ፣ የወደፊቱንስ የሚያመላክት ጽሑፍ/ሐውልት ነው ለማለት አንችልምን? (አዳም ረታ)፡፡ ስለ እንጀራ አመጣጥ ሚቶሎጂ ደግሞ እንዲህ ያትታል… “በአንድ አምላክ መመለክ ከመጀመሩ በፊት የኖሩ ማኅበረሰቦች ለእያንዳንዱ ፍጡር እና ባሕርይ የሚያብራሩት ትረካዎች ነበሯቸው፡፡ ኃላፊነትን ሁሉ ጠቅልለው ለአንድ አምላክ ከመስጠታቸው በፊት በነበረው በዚያን ዘመን የፍጡራን እና የፍጡራኑ ግብር በጠቅላላው በሚቶችና በአፈታሪኮች የማብራራት ልማድ ነበራቸው፡፡ ከ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ ጋር ባደረግሁት ቃለ ምልልስ የጤፍን አመጣጥ የሚያብራራ አፈታሪክ ነገር እንደማይጠፋ ተናግሬያለሁ፡፡ (ያኔ ማግኘት አልቻልኩም ነበር እንጂ)፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በለስ ቀንቶኝ ጤፍ እንዴት የኢትዮጵያዊያን ዋና ምግብ ሊሆን እንደቻለ የሚያብራራ አንድ ታሪክ አነበብኩ፡፡ አሁን የታሪኩን ዕውነተኛነት ጥያቄ ውስጥ አላስገባም፡፡ ሁሌም ቢሆን ሚቶችን ስናነብ የምናደርገው ስለ ዕውነተኛነታቸው መጨነቅ ሳይሆን ሚስጥራቸውን ፈልፍሎ ለማውጣት መጣር ነው፡፡ የተለያዩ ሕዝቦች ከላይ ሲታዩ እርባና ቢስ የሚመስሉ ጥያቄዎችን የሚመልሱባቸው ተረኮች እንዳሏቸው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ለምንድን ነው ቀበሮ ጭራ የበዛው ጅራት ያላት? ውሻ እንዴት ለማዳ ተደረገ? ጨረቃ ለምን በየወሩ ትመጣለች? ሰው የተፈጠረው እንዴት ነው? የጤፉ ጉዳይ ለየት የሚያደርገው የተወሰነ አመክንዮአዊ ድባብ አለው፡፡ የሆነ ሊታመን የሚችል ነገር፡፡ እንግዲህ ይሄ ታሪክ የተከሰተው ከክርስቶስ በፊት 1500 አካባቢ ነው፡፡ ክስተቱም በእውኑ ዓለም ከነበረ ሰው ጋር ተያያዥ ነው፡፡ ይሄውም ሰው ኢስዬል፣ አጋቦስ (የንግሥና ሥም) የሚባል ኢትዮጵያዊ ንጉስ ነው፡፡ (‘አፄ’ የሚለውን የማዕረግ ሥም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመ ንጉስ)፡፡ ሌላኛው ስሙ ሰንደቅ አላማ ይባላል (ብዙ ስሞች አሉት)፡፡ ሰንደቅ አላማ ዘንዶ ንጉስ ነበር፡፡ (ይህቺ የዘንዶ አፈታሪክ ዓለም አቀፋዊ ናት)፡፡ ከሕይወት ታሪኩ እንደምንረዳው፤ ይህ ሰው ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ‘ሳይንቲስትም’ ነበር፡፡ ዘመሚትን፣ በቅሎን፣ የሜዳ አህያን የመሳሰሉ እንስሳትን ተያያዥነት ያላቸውን ዝርያዎች በማዳቀል እሱ እንደፈጠራቸው ይነገራል፡፡ ሰንደቅ አላማ በተፈጥሮ ላይ ይመሰጥ ስለነበር፣ የራሱ የሆነ የአትክልት ቦታ እና የእንስሳት ማቆያ ነበረው፡፡ ረዥም ዕድሜ ለመኖር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ለመፈልሰፍ ታድሎም ነበር፡፡ በዚህም ከ425 ዓመታት በላይ መኖር ችሏል፡፡ የሚበላውና የሚጠጣው ሁሉ ከሰው የተለየ እንደነበር ይነገራል፡፡ የሚጠጣው ውሃ ከአለቶች መካከል ከሚፈልቅ ምንጭ ይቀዳል፤ ‘የሕይወት ውሃ’ ነበር የሚባለው፡፡ እያደር ወጣት የሚያደርግ ኃይል ያለው ድንጋይ ላይም ይተኛ ነበር፡፡ ሰንደቅ ዓላማ 425 ዓመታትን ከኖረ በኋላ ግን ሕይወት ሰለቸችውና መሞት ፈለገ፡፡ አንዲት ወጣት ልዣገረድ እንድትገድለውም አደረገ፡፡ አፄውን የገደለችው ይህች ወጣት ኋላ ላይ ንግሥት ማክዳ/ሳባ ሆነች፡፡ የቀደመ ስሟ ኢተያ/እትዬ/እቴጌ ነበር… ሳባ እንግዲህ ‘እቴጌ’ ተብሎ ለመጠራት የመጀመሪያዋ ንግሥት ነች፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ አላለቀም፡፡ እሱ ከሞተ በኋላ ሳባ ንግሥት ሆነች፡፡ በዘመነ መንግሥቷም ረሃብ በመላ አገሪቷ ተስፋፋ፡፡ የተራቡ ወገኖቿን መመገብ ያቃታት ሳባ፣ የሰንደቅ ዓላማ መቃብር ዘንድ ሄዳ አነባች፤ ፀሎት አደረሰችም፡፡ በሕልሟም እግዚአብሔር ቀርቦ በንጉሱ መቃብር ላይ ከሚበቅለው ሣር በሚገኘው ፍሬ ሕዝቧን እንድትመግብ ነገራት፡፡ እንደተነገረችው አደረገች፡፡ ያ የሣር ፍሬ ጤፍ ነበር፡፡ ‘ጤፍ’ ማለት ትርጉሙ ‘ጣፋጭ’ እና ‘የተትረፈረፈ ምርት’ ማለት ነው፡፡ ጤፍ ዝናዋ ገናን የሆነ ፍሬ ነበረች፤ ስለ እሷ በመስማት ብቻ ንጉስ ዳዊት የምወድስ ግጥም ጽፏል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ባዮሎጂስት የነበረ መሆኑ የጤፍ ግኝት የአጋጣሚ ነገር አይመስልም… ምናልባትም ንጉሱ ራሱ ይሆን ይሆናል መጀመሪያም ጤፍን ያገኘው፤ የማክዳ ተረት ነጋሪዎች ይሆናሉ የፀሎቷን፣ ሕዝብ የመመገቧንና የእግዜርን ነገር ያከሉበት፡፡ እንደው ነገሩ እንዲህ እንኳ ባይሆን፣ ጤፍ እንዲህ ባለ ንጉስ መቃብር ላይ መብቀሏ በራሱ እየሞተ ካለ የንጉሱ ገላ ረዥም ዕድሜ የመኖር ምስጢርን እየወረሰች ይመስልባታል”፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለች የተጀመረችው ጤፍ እንግዲህ ረዥም ዕድሜ መቆየት ብቻ ሳይሆን እንጀራ በመሆን ዘላለማዊ ሆናለች፡፡ አዳምም እንጀራ ምግብ ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራ የአጻጻፍ ስልቴን የቀዳሁበት ሞዴል ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራ ዘይቤ ብቻ ሳይሆን እናት ዘይቤም (root metaphor) ነው ይላል፡፡ “እናት ዘይቤ ማለት…” ይላል አዳም “እናት ዘይቤ ማለት በአንድ ቋንቋ ወይም ባሕል ውስጥ በጥልቅ በመስረጉ ዘይቤ መሆኑ ከነጭራሹ ልብ እንኳ የማይባል ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከውስጡ ሌሎች ዘይቤዎች የሚወጡበት አንድ ዘይቤ ነው ሲሉ ይተረጉሙታል”፡፡ መቸስ እንጀራ ከዕለት ዕለት ተግተን የምናላምጠው ቋሚ ምግባችን እንደመሆኑ እንደ አዳም ቀንቶን “በሆነ ዓይነት ስነ-ውበታዊ ልምድ” ውስጥ ካላለፍን በቀር አንድም ጊዜ እንኳን አይደለም ሚስጥራዊ ዘይቤነቱ አመጣጡ እንኳን አስጨንቆን አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው እንጀራ እናት ዘይቤ (root metaphor) ነው የሚለው አዳም፡፡ አዳም ይቀጥላል… “የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ዝርዝር ጉዳዮቻችንን በዚህ የእንጀራ ዘይቤ ማብራራት እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄን የምናደርግበት አንዱ መስክ ልቦለድ በመጻፍ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እየሠራሁበት ያለውን ይሄ ዓይነቱን አጻጻፍ ደግሞ ‘ሕጽናዊነት’ እለዋለሁ”፡፡ “ሕጽናዊነት”፡ የቃሉ አፈጣጠር/አመጣጥ ሕጽናዊነት እና ዘይቤ ምን አገናኘው ብሎ የሚጠይቅ ይኖር ይሆናል፡፡ ‘ሕጽን’ የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሁለት ፊደሎች መካከል ያለው ክፍተት ማለት ነው፡፡ ጽሑፍ ሊነበብ የሚችለው ይሄ ባዶ ቦታ በየፊደላቱ መካከል በመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ በፊደል ገበታ ውስጥ ያሉት ክፍት ቦታዎች ደግሞ ማሕጸን ይሰኛሉ፡፡ ሁለቱም ቃላት የተወሰነ የትርጉም መመሳሰል አላቸው፡፡ እነኚህ ባዶ ቦታዎች ከእንጀራ ዐይን ጋር በይዘት መመሳሰል እንዳለባቸው ነው የሚገባኝ፡፡ የሕጽናዊነት ዓላማ ይሄንን ባዶ ቦታ መሙላት ነው፡፡ የሚነበበው ነገር መሙያው ነው፤ አዲሱ ጽሑፍ ማለት ነው፡፡ ከ”አዲስ ነገር” ጋዜጣ ጋር ባደረግሁት ቃለ ምልልስ ይሄንን ነገር ‘ኢንተርቴክስቹዋሊቲ’ ብዬ አስቀምጬው ነበር፡፡ ይሄን ያደረግኩት ግን በወቅቱ ሕጽናዊነትን የሚያክል ተስማሚ ቃል ባለማግኘቴ ነበር፡፡ ገሃዱን ዓለም በማንፀባረቅ ረገድ አንድ ወጥ የሆነ ትረካ ሕጽናዊ ከሆነው ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚለው ጥያቄም ነበር፡፡ ከ”እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” [እ.ሎ.ሽ.] በፊት የጻፍኳቸውን ታሪኮች አሁን ላይ ሆኜ ሳያቸው የተሟሉ አይደሉም፡፡ ሕጽናዊነት በዚህ ረገድ የቀድሞ እኔነቴን በራሴ የለካሁበት/የሄስኩበት ስልት ነው፡፡ (“Hisinawinet” in this case becomes a critique of my earlier self) ሕጽናዊነት የአንዱ ከሌላው መያያዝ ነው… ራሳቸውን እንደ ደሴት የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ ከላይ ሲታይ የተለዩ ይመስሉ ይሆናል፤ በጥልቅ ላጠናቸው ግን ሰዎች እርስ በራስ የተጠላለፉ/የተቆራኙ/የተዛመዱ ናቸው… በዘር፣ በቋንቋ፣ እልፍ የባሕል እሴቶችን በመጋራትም”፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸውን መረባዊ ግንኙነት ማሳየት የሕጽናዊነት አንዱ ግብ መሆኑ በአዲሱ መጽሐፍ “መረቅ” ውስጥ እንዲህ ተቀምጧል፡ “በሕጽናዊነት አመለካከት በሰው ልጆች መሃል ያለው የግንኙነት መስመር ቀጥተኛ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው በግልጽም ይሁን በሕቡዕ መረባዊ መሆኑን ማንሳት ነው” (ገጽ 599)፡፡ አዳም ቀጥሏል… “የሕዳግ ማስታወሻ የሚያገለግለው እነኚህን መረባዊ ግንኙነቶች ጠቅልሎ በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት ነው፡፡ በእ.ሎ.ሽ. ከበደ ሚካኤልን ሳጣቅስ የእሳቸውን ፖለቲካዊ አቋም እደግፋለሁ ማለት አይደለም ወይም ደግሞ ባሕልን እንደሳቸው ሁሉ በወግ አጥባቂ ዐይን እቃኛለሁ ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ የእሳቸውን ያክል መልከ መልካም ነኝ ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ሎሚ ሽታን ወይም የፍቅረስላሴን ልጅ ታደሠን ያውቁታል ማለት አይደለም ወዘተ… የባሕል መረቡ በቀስታ ተስፋፍቶ እዚያች ደረጃ ድረስ እንዴት እንደሚደርስ ለማሳየት ብቻ ነው፡፡ (showing how cultural network can percolate and present itself to that minute depth) ታዲያ ከሌላ ደራሲ ሥራ የተወሰደን አጭር ተረክ በአንድ ወጥ በሆነ ልቦለድ ውስጥ መጠቀም አዲሱን ታሪክ የፊተኛው ጥገኛ፤ በራሱ መቆም የማይችል፤ ክፍተት ያለበት አያደርገውም? ብሎ ለሚጠይቅ ቅን አንባቢ፣ አዳም ይሄንን ይመልሳል… “እቴሜቴ ውስጥ ያካተትኩትን ያን የከበደ ሚካኤልን ተረት [በማር ጠብታ ውስጥ ስለሰጠሙ ሕዝቦች የሚተርከውን] ቆርጬ ባወጣው እንኳ ልቦለዴ ያለምንም የይዘትም ሆነ የሴራ እንከን ፍሰቱን ይቀጥላል”፡፡ አንዳንድ የሕጽናዊነት መገለጫዎች ከሕጽናዊነት መገለጫዎች አንዱ ኢንተርቴክስቹዋሊቲ ነው፡፡ ኢንተርቴክስቹዋሊቲ ማለት በቀላሉ በአንድ ትረካ ውስጥ ሌላ ገጠመኝ፣ ሌላ ልቦለድ፣ የታሪክ አጋጣሚ ወዘተ ሲጠቀስ ማለት ነው፡፡ የዚሁ ትርጓሜ ተመሳሳይ የሆነው ኢንትራቴክስቹዋሊቲም መነሳት ይኖርበታል፡፡ የሁለቱ ልዩነት በአጭሩ ሲቀመጥ፤ የመጀመሪያው አንድ ደራሲ የሌላን ደራሲ/ገጣሚ ሥራ (የዕውንም ይሁን ምናባዊ)፤ ከዕውነታው ዓለም የተቀዳ ገጠመኝ፤ የጋዜጣ ጽሑፍ ወዘተ ሲጠቀም ሲሆን ሁለተኛው ድሞ አንድ ደራሲ የራሱን ቀደምት ሥራዎች ሲያጣቅስ ማለት ነው፡፡ “ብዙ የተማረ ዜጋ/ብዙ ያነበበ ዜጋ ባላቸው አገሮች ዋቤ ሳይጠቅሱ (የዕውነት ያለን) ጽሑፍ ማጣቀስ የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም ያ ጽሑፍ የሌላ ሰው እንደሆነ ይሄኛው ደራሲ ግን እንደ ወሽመጥ እየተጠቀመው ወይ ደሞ እየተረበው እንደሆነ አንባቢው ያውቃል፡፡ በእኛ አገር ግን አለመግባባትን ለማስወገድ በሕዳግ ማስታወሻ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ አለመግባባቱም ሁለት ዓይነት መልክ ሊኖረው ይችላል፡ አንደኛው አንዳንድ አንባቢ (በቅን ልቦናም ይሁን በተንኮል) ያ የተወሰደው ጽሑፍ የተሰረቀ ነው ብሎ ሊያስብ ስለሚችል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንባቢው የተጣቀሰው ጽሑፍ ዓላማ ላይገባው ስለሚችል ነው፡፡ አንባቢው ይሄን መረዳት ካልቻለ ደግሞ አንዱ የኢንተርቴክስቹዋሊቲ ግብ ልቦለድን ወደ ዕውነታዊ ክዋኔ ማምጣት (bring fiction as experience) ተኮላሸ ማለት ነው”፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን በምሳሌ እንመልከት፡፡ ደራሲው በእ.ሎ.ሽ. “በማር ጠብታ ውስጥ ስለሰጠሙ ሕዝቦች አንብቤያለሁ” ሲል በሕዳግ ማስታወሻ የከበደ ሚካኤል ታሪክ እንደሆነ ገልፆዋል፡፡ በ”መረቅ”ም “ግቡ እናንተ ተስፋ ያልቆረጣችሁ” (ገጽ 73) ሲል ከዳንቴ “ዲቫይን ኮሜዲ” እንደወሰደው ጠቅሷል፡፡ በሌላ መልኩ ማንም ያነበበው፤ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ታሪክ ነው ብሎ በማሰብ፤ ማንም “ባለ ቅን ልቦና” ወይ “ሴረኛ” የተሠረቀ (plagiarized) ነው እንደማይለው በማመን፤ እንዲሁም ልቦለድን ወደ ዕውነታዊ ክዋኔ ለማምጣት (to bring fiction as experience) የፊታውራሪ መሸሻን፤ የሰብለን፣ የበዛብህን እንዲሁም የእንቆጳን ታሪክ (አንዳንድ ለውጦች ተደርገውባቸው) እንዲሁ በ”መረቅ” ውስጥ ተጠቅሟቸዋል፡፡ አዳም ከቲዮሪ ባሻገር በሥራዎቹ ኢንተርቴክስቹዋሊቲን ብቻ ሳይሆን ኢንትራቴክስቹዋሊቲንም ይጠቀማል፡፡ በየመጽሐፎቹ ውስጥ እዚህም እዚያም የሚገኙት የግጥምና የዘፈን ስንኞች፤ ቦታቸውን እንዳገኙ ሁሉ ስክት የሚሉት የግዕዝ ሀረጋት፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፤ ምናባዊ ማጣቀሻ መጻሕፍቱ እና የጋዜጣና የመጽሔት ቃለ ምልልሶች ወዘተ የኢንተርቴክስቹዋሊቲ አብነቶች ናቸው፡፡ በሌላ መልኩ በአዳም ልዩ ልዩ መጻሕፍት መካከል እንዲሁም በአንድ የአዳም መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ትረካዎች መካከል ያሉ እንደ ዘሀ የቀጠኑ የግንኙነት መስመሮች የኢንትራቴክስቹዋሊቲ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ”ሕማማት እና በገና” ውስጥ ያለው ትንሽ ልጅ (የብርሃኑ ጓደኛ) “አለሙ” የተሰኘ የቤት ስም አለው፡፡ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” (ይ.መ.ያ.መ.) ላይ ያለው ዋና ገፀ ባሕሪ “አለሙ” ይሰኛል፡፡ ሁለቱም የሸማኔ ልጆች መሆናቸው የአጋጣሚ ነገር ይመስላችኋል? በ”መረቅ” ውስጥ በጨረፍታ ዳሰስ የተደረገችው ሊሊና የዚታዎ ሾፌር የሆኑት ጓደኛዋ ዘርአብሩክ በኩሳንኩስ ውስጥ አንድ የታሪክ አንጓ ተሰጥቷቸው አልተተረኩምን? የ”ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገዱ” ሸገኔ “መረቅ” ውስጥ ተጠቅሶ የለምን? እ.ሎ.ሽ. “ጉርሻ ተሻጋሪ ነው” በምትል ቀጭን መስመር ከ”መረቅ” አልተዛመደም? በይ.መ.ያ.መ. በእያንዳንዱ ትረካ ላይ ብቅ የሚለው ያ ጃን አሞራ በታሪኮቹ መካከል ትስስር አልፈጠረም? በእ.ሎ.ሽ. ውስጥ የሚገኙ ታሪኮችስ አንዳቸው ከሌላቸው በገጸ ባህርያቱ የትውውቅ እና የዝምድና መረብ የተጠላለፉ አይደሉ? “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” ውስጥ “ለብሮት” የሚለው ታሪክ ገጸ ባሕሪ ትርንጎ፤ በ”ሕማማት እና በገና” “የሳር ልጆች” ውስጥ ተመልሳ አልመጣችም? ብዙ ብዙ፡፡ ይሄ እንግዲህ በእኔ አቅም ሊታይ የቻለ ትስስር ነው፤ ጊዜውን ሰጥቶ በጥልቀትና በጥንቃቄ ለሚያጠናው ሰው ከዚህም በላይ ግንኙነቶችን መጥቀስ እንደሚቻል እርግጠኛ ነኝ፡፡
የሕጽናዊነት መሠረታዊያን “የአብሮነት ቃል” ከተባለ መጽሔት ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ አዳም ረታ “የሕጽናዊነት ስነግብር ንጥረ ነገሮች እነዚህ ናቸው” ብሎ ያስቀመጣቸው አራት የሕጽናዊነት መሠረታዊያን ነበሩ፡፡ እነኚህ አራት ነጥቦች የሚያስረዱትም፡- “1/ ሁሉ ነገር በታቀደና ባልታቀደ ግንኙነት ውስጥ መሆኑን 2/ ሁሉ ነገር በታቀደና ባልታቀደ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በታቀደና ባልታቀደ ለውጥ ውስጥ መሆኑን 3/ አሁን ተነጣጥሎ የተቀመጠ የሚመስለው ቢያንስ አንድ የጋራ የግንኙነት መስመር እንደማያጣ (ከአዳምና ከሄዋን ተገኘን ማለት)(ሙሉኩሌው ወይም የፀ ሐይ ስርዓት ከአንድ ታላቅ ፍንዳታ (big bang) ተፈጠረ እንደማለት) 4/ አንድ ወጥ አጭር ታሪክን ወይም ረዥም ልብ ወለድን የተሳካ ማለት ጎደሎውን መቀበል መሆኑን፡፡ ለአባባል ሕጽናዊነት ሁሉን ነገር ቀናንሰን ስናነበው ግንኙነት አለው፡፡ ዋናው የስነ ጽሑፍ አላባው ይሄ ነው፡፡ እንጀራ ውስጥ የተቀበረው ሚስጥር ይሄ ነው፡፡ ከላይ ሲያዩህ ነጠላህን ያለህ ይመስልሃል ግን አነሰም በዛም፣ አወኩትም አላወኩትም፣ ገባኝም አልገባኝም፣ ተከሰተ አልተከሰተ መረብ ውስጥ ነኝ ማለት ነው˝ (አዳም በ”እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ግንኙነት በባለ ሁለት ወይም ባለ ሦስት ዲሜንሽናል ግራፍ ማስቀመጥ እንደሚቻል ከተናገረ በኋላ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ታሪኮቹን/ የገጸ ባሕሪያቱን ግንኙነት በባለ ሁለት ዲሜንሽናል ግራፍ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ ውጤቱም በምስሉ ላይ እንደሚታየው የእ.ሎ.ሽ. ገጸባሕሪያት ግንኙነት መረባዊ እንደሆነ በተጨማሪም በታቀደና ባልታቀደ ግንኙነት ውስጥ መሆኑን አረጋግጧል)፡፡ ሕጽናዊነት እና ትውስታ መኖር ማስታወስ ነው፡፡ ጥበብ ደግሞ የማስታወሶች ሁሉ ቁንጮ፡፡ To live is to remember. Art is the highest form of remembrance. (እ.ሎ.ሽ.) “የሕጽናዊነት ዘፍጥረት ጤፍ እንጀራን እንደ ትውስታ (memory) ከመቁጠር ይነሳል፡፡ የሆነ ዓይነት ትውስታ ጤፍ ውስጥ እንደተከማቸ እገምታለሁ፤ አምናለሁም፡፡ ሕጽናዊነት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ይሄንን ትውስታ ቆፍሮ ማውጣት ነው”፡፡ The genesis of Hisinawinet is Tef Injera as memory. I assumed and believed that memory is stored in the injera. What Hisinawinet does is retrieve it. What is stored is in a spatial form. What we particularly retrieve is connectivity at the center of existence. We are teasing our pagan past in search of fruitful meaning. Hisinawinet is a robust technology of writing fiction (at least in my current case). Definitely, it is a technology of connectivity, of empathy and positive liaison. “ማንኛውም ልቦለድ አያልቅም፡፡ ማለቁ ምትሃት ነው (ምሉዕ አይደለም)፡፡ የመስፋፋት ድብቅ ኃይል (ፖቴንሽያል) አለው፡፡ ይሄ እኔ የምጠቅሰው መስፋፋት ግን በመለጠጥ የሚመጣ አይደለም፣ ቢያንስ በእኔ የግል ትውፊት፡፡ መለጠጥ ግራና ቀኝን ያሳያል እንበል--ከመጀመሪያውና ከመጨረሻው ይዞ (ልክ እንደ ላስቲክ) በመጎተት ማስፋት፡፡ እኔ የምለው መስፋፋት ከመሃል ልክ እንደ ወሽመጦች (ሕጽኖች) አቢይ ምዕራፎች በማስገባት ‹‹ያመለጡ›› አዳዲስ የእንጀራ/ እንጆሪ ዐይኖችን (ታሪኮችንና መረጃዎችን) በማስገባት መስራት ማለቴ ነው፡፡ … ስለዚህ እኔ ስለሚስፋፋው ልቦለድ ሳወራ ስለስግሰጋ ማለቴ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወሽመጦች ተዋረድ ሳይጠብቁ ከተጠቀሱበት ምዕራፍ ወጥተው የበላይ ነን ሊሉ ይጥራሉ፡፡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተረሳ ነገር ከምናስታውሰው የበለጠ የበላይነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሕጽን ከዝንጉነት መውጫ መሣሪያ ልትሆን ትችላለች፡፡” ግራጫ ቃጭሎች፤ እንደ መግቢያ፡፡ (አፅንኦቱ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ነው)፡፡ “ሕጽናዊነት የሚነግረን ነገር ቢኖር ወደ ደራሲው፣ ወደ ገጸባሕሪውና ወደ አገሪቷ ትውስታዎች በጥልቅ መግባትና እነዚህን ማገናኘትን ነው፡፡ ትርጉሙም የሚገኘው በግንኙነታቸው ውስጥ ነው”፡፡ ስለ ግንኙነት በምሳሌ ለማስረዳት አዳም በአንድ ወቅት በቪዲዮ ያየውን ቃለ ምልልስ ቀላል አብነት ያደርጋል፡፡ አዳም በዚህ ቃለ ምልልስ ውስጥ ያዳመጠው/ የተመለከተው አፄ ኃይለሥላሴ በእስር በነበሩበት ወቅት ከጠባቂያቸው ወታደር ጋር ያደረጉትን ጭውውት ነው፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን አፄው ወታደሩን ጥያቄዎች ይጠይቁታል… ስሙን፣ የአባቱን ስም፣ የትውልድ ቦታውን ወዘተ፡፡ ወታደሩ ስሙንና የአባቱን ስም ነገራቸው፡፡ የተወለደውም ሐረርጌ ውስጥ ኤጀርሴ ጎሮ እንደሆነ ሲነግራቸው “የአያትህ ስም እከሌ አይደለምን?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ ኃይለሥላሴ የተወለዱት ኤጀርሴ ጎሮ ነበርና የወታደሩን አያት በአካል ያውቋቸዋል፡፡ ወታደሩ ዕውነትም ኃይለሥላሴ የጠሩት ስም የአያቱ ስም መሆኑን አረጋገጠላቸው፡፡ ከዚያም ወታደሩ ድብርት ያዘው፡፡ ታዲያ አዳም ይሄን ምሳሌውን ሲያብራራ እንዲህ ይላል፡- “አሁን ደግሞ ኃይለሥላሴ እስር ላይ አልነበሩም፤ ወታደሩም አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ቢራ እየጠጣ ነበር ብለን እናስብ፡፡ እርስዎም ግሮሰሪው ውስጥ ነበሩ፡፡ እነኚህ ሁለት ሰዎች በአያትዬው ትውስታ አማካኝነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል ብለው ሊገምቱ ይቻልዎታል? ሕጽናዊነት በምናቡ ዓለም ውስጥ ይሄንን ነው የሚያደርገው /That is what Hisinawinet does in a fictional world”፡ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጅ ባሕል ውስጥ ጠፋ/ተረሳ የተባለ ጉዳይ አብዛኛውን ጊዜ ተመልሶ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ እንደጠፋ የሚታወቅ ሲለካንስ የተባለ የዓሳ ዝርያ አለ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ በ1938 ሊታይ ችሏል፡፡ “የሰውን ተፈጥሮ ከምንጩ ለመረዳት (በእኛ ሁኔታ አገርና ማሕበረሰብን) የቆዩ መዛግብትን ትርጓሜ በሰፊው ይሠራል፡፡ ፍሮይድ በኤዲፐስ ያደረገው ይሄንን ነው፡፡ አንድን ድራማ ነው የተነተነው (analyze ያደረገው)፡፡ ያንግ ደግሞ ሕልሞችን፣ አፈታሪኮችን/ተረቶችንና mandala-ዎችን፡፡ ፍሮይድ የሠራውን ነገር ከፖሊዮግራፊ [ጥንታዊ የፊደል አጣጣል ስርዓቶችንና ታሪካዊ ሰነዶችን የማጥናት ዘዴ]፣ ከቁፋሮ፣ ከትርጉም ሥራ እና ከጥንት ቋንቋዎች ጥናት ጋር ያወዳድረዋል፡፡ በርካቶች ዛሬ ላይ የተከሰተን ኩነት ለማብራራት መጻሕፍትን ያጣቅሳሉ፡፡ ሆኖም መጻሕፍት በትርጉም ልዩነት ሰበብ ተበክለዋል ወይም የትርጉም መዛነፍ ሰለባ ናቸው/ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የቀደሙት ኢትዮጵያዊያን/ሰንደቅ ዓላማ/ ያደረገው ለሁሉም ወገን ገዢ የሚሆን ፅላት (iconic) ወገንተኝነትንና አይዲዮሎጂዎችን የሚደመስስ “ዳቦ” መፍጠር ነበር፡፡ እንጀራ በየዕለቱ ይጠቀሳል፤ በየዕለቱ ፉክክር ውስጥ ይዶላል፡፡ ታዲያ የዚህን ግኝት የተደበቀ ምስጢር ስለምን አንበረብርም? በጠቅላላው የባሕል ዝግመተ ለውጥ ውስጥ እንጀራ የሚይዘው ቦታ ትልቅ ነው፡፡ የአበው ትውስታዎች በእንጀራ ውስጥ ተሰግስገዋል፤ እንጀራ ደግሞ ሁሉም የሚጋራው ነገር ነው፤ ደካማውም ጠንካራውም፡፡ በሌላ አነጋገር ታሪክ በሁሉም ዜጋ አምሮቶችና ፍላጎቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ የሚጨበጥ የሚዳሰሰው ማስረጃ (የድንጋይ ላይ ፅሑፍ፤ ወፋፍራም ብራና፤ ቋንቋ) በጦርነት እና በፕሪጁዲስ በንኖ ሲጠፋ ረቂቋ እንጀራ ግን በገበሬዎች፣ በሸክላ ሠሪዎች፣ በልዣገረዶች፣ በማቡኪያዎች… ጀርባ ታዝላ ዛሬን አይታለች”፡፡ The place of injera in the general process of cultural evolution is important. The memories of the old were embedded in the injera, an element which both the powerful and the weak shared. In other words, History was embedded into the need and necessities of everyone. “ሕጽናዊነት የሚያደርገው ትውስታዎችን ቆፍሮ ማውጣትና እነዚህን ትውስታዎች ክቦች፣ መረቦችና ስድስት ጎኔዎች ወደሚመስሉ ቀላል ቅርፆች ጨምቆ ማቅረብ ነው”፡፡ What Hisinawinet does is retrieve these memories by abstracting them into ‘simple forms’ of circles, labyrinths and hexagons. አበው እና ሕጽናዊነት “የጥንት ሰዎች ሙሉዕ የሆነ ሕይወት ነበራቸው፡፡ ማለት የሚያደርጉት፣ የሚያስቡትና የሚያመልኩት ሁሉ በአንድ ወጥ የፍልስፍናና እና የእምነት ሥርአት የታገገ ነው፡፡ ታዲያ እንጀራ ከምግብነቱ ሌላ ይሄንን ተንተርሶ ምን ተጨማሪ መልዕክት (ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ታሪካዊ) ሊኖረው ይችላል? ለእኔ ይሄ “ዳቦ” ምን ያወራልኛል? እንጀራ ራሱ ልክ እንደ መጽሐፍ ወይም እንደ ሃውልት ታሪክ ማስተላለፊያ ወይም የፍልስፍና ማስተላለፊያ ከሆነስ? …ብዙ ጊዜ ሰዎች ሃሳባቸውን በቋንቋ (በተረት)፣ በዕብነታ-ፅሁፍ፣ በብራና፣ በወረቀትና በእንጨት ላይ ታሪካቸውን ብቻ ሳሆን ራዕያቸውንም ይፅፋሉ” (አዳም “የአብሮነት ቃል” ለተሰኘው መጽሔት ካደረገው ቃለ ምልልስ የተወሰደ) “ሕጽናዊነት ስለሚታይ እና የማይታይ ግንኙነት (connectivity) የሚያስረዳ እሳቤ ነው፡፡ አበውን ሳስብ የሚገባኝ የምንበላውን ነገር እና ስለ አበላላችን ጭምር በያንዳንዱ ነገር ውስጥ ምስጢር እንደሚተክሉ ነው”፡፡ “አበው ይሄን የተገናኝነት ነገር ሲያገኙ/ሲፈለስፉ ሕይወታችንን እናቆይበት ዘንድ የምንበላው እንጀራ ብቻ አይደለም ያወረሱን፤ ጥልቁን የዩኒቨርስ፣ የአገርና የግለሰብ የተገናኝነት ጽንሰ ሐሳብ ጭምር እንጂ”፡፡ When the ancients discovered/ invented this form they not only bequeathed to us the “Injera” as a font of sustenance, but also a transporter of the deep and necessary understanding of the concept of connectivity in the universe, the nation and the self. “እንጀራን አቅርበን ብናየው ዐይኖቹ ባለ ስድስት ጎን ጉድጓዶች ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የሰው ልጅ ቆዳ ሴሎች ቅርጽ ነው፣ የደም ሴሎች፣ እንጨት፣ ብረት፣ አፈር ወዘተ ይሄው ቅርፅ አላቸው፡፡ ይሄን የመሳሰለው ሙሉኩሏዊ (universality) የቅርጽ መመሳሰል እንጀራን የሆነ ትዕምርታዊ ኃይል (symbolic power) እና የሆነ ዓይነት የታቀደ/በዕውቀት የተደረገ/ ዓላማ (a sense of planned purpose) ይሰጠዋል”፡፡ በተጨማሪም “አበው በዩኒቨርስ ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ አንዱ ከሌላው የተገናኙ መሆናቸውን አውቀው በእንጀራ ውስጥ በሚስጥር ማስቀመጣቸው አዲስ የልቦለድ ቅርጽ ዲዛይን ለማድረግ ያገለግል ይሆናል፡፡ እንጀራ የአንድ ሀሳብ ትውስታ ነው፤ ህብር ያለው ተገናኝቷዊነትን የማግኘት/የመፈልሰፍ ሀሳብ”፡፡ The realization of the ancients about the interconnection of the universe as coded in the injera can be an instrument in designing a fictional form. Injera is the memory of an idea; the idea of discovering or inventing a harmonious connectivity. “አፄ ሰንደቅ ዓላማ እንስሳትን ሲያዳቅሉ ያደረጉት ቢኖር ከዚያ በፊት ተገናኝተው የማያውቁ ዘረመሎችን አገናኝተው ከዚያ በፊት ያልነበረ አዲስ ችሎታ/መለያ ባሕሪ መፍጠር ነበር፡፡ ይሄ ማለት በቸልታ የጠፉ ወይም ሆን ተብሎ የወደሙ የግንኙነት መረቦችን መፈለግ አለብን ማለት ነው”፡፡ ሕጽናዊነት ልዩ ተአብ ነውን? “ልቦለዶቻችን በአብዛኛው ቀጥታዊ ወይም ክባዊ (linear or circular) እንደሆኑ ብዙ ጊዜ ሲባል ሰምተናል፡፡ እኔ ደግሞ ሁሌ በተቃራኒው ቀጥታዊ ትረካ ዕውነታን ለማሳየት ጥንካሬ የለውም ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ሰው ደግሞ የቀጥታዊ ትረካ ስልቶች አቅም ላይ ጥርጣሬ ካለበት ሌላ የተለየ ጂኦሜትራዊ ዘይቤ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ የ1974 የኢትዮጵያ አብዮት የቀጥታዊ ተረክ ሞት መጀመሪያ ነበር፡፡ ያኔ የተፈቱት ብትንታኞች እስካሁን ድረስ በማንኛውም ዓይነት የሕይወት እንቅስቃሴያችን ላይ ተፅዕኖ ሲያሳርፉ ይታያል፡፡ (The fragmenting elements unleashed then are still working their way through all aspects of life) በዝብርቅርቅ ውስጥ ያለ ማሕበረሰብ ደግሞ ቀጥታዊነት የሚስማማቸው ግለሰቦችን ሊወልድ አይችልም፡፡ እነኚህን ዕውነታዎችና ሂደቶች ለማሳየት ደግሞ ሌላ መንገድ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ዝብርቅርቅ የሚገኘው ጂኦሜትሪያዊ ዘይቤ ደግሞ መረባዊ አወቃቀር ወይም ውስብስባዊ ነው፡፡ ታዲያ ይሄንን ለመወከል ከእንጀራ በላይ ምን ተገቢ ነገር አለ?” እንጀራን መሠረት ያደረገውን ይሄን “የአፃፃፍ ስነግብሬን (method) ሕጽናዊነት እለዋለሁ፡፡ የምናገርለት ጉዳይ በእኛ አገር አዲስ ቢሆንም በሌሎች አገሮች የተሠራበት ወይም እየተሰራበት ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ በኩል በሰፊው ልናገርለት የምችል የአለቃ ግንዛቤ የለኝም፡፡ ግን የአፃፃፍ ስልቴን ከመግለጫዎች በፊት በድርጊት ለማምጣት ሞክሬያለሁ፡፡ ይሄም የራሱ መሰረት አለው፡፡ በ”ግራጫ ቃጭሎች መግቢያ ላይ የሞከርኩት መንደርደሪያ ቢሆንም ቦታው እንዳልሆነ የተቹኝ አሉ፡፡ የሆነ እውነትነት አለው፡፡ ምናልባት ቆየት ብዬ ስለ ስነግብሬ በሆነ መልክ ለአንባቢያን ለብቻው ማቅረብ እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ እኔ በተመጠነ ደረጃ በፅሁፍ ወይም ስርዓት ባለው መንገድ ግልፅ ባላደርገውም ሕጽናዊነት አንዳንድ የሚያዋጣ አቅጣጫ ሊይዝ እንደሚችል ከፍንጭ በላይ መከራከሪያ አለኝ፡፡ አንዱ ድርጊቱ ነው፡፡ “ግራጫ ቃጭሎች”፣ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” እና “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ድርጊቶቹ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ኮስታራ ከሆነ ወይም ከተባ የስነፅሁፍ ወይም የባሕል ሂስ ካለበት ሕብረተሰብና ልብወለድ ሳይሆን ንዑስ ዘውጎች ያልተሰሙለት ዘመናዊ ከተባለ የስነፅሁፍ ባሕል የተመዘዝኩ ነኝ፡፡ ይሄ እጥረት በሆነ መልክ ድጋፍ ያጣሁ ደራሲ ያደርገኛል፡፡ የራሴን ፍልስፍና ስናገር በአገራችን የመጻፍ ካርታ ላይ ከማንና የት ጋ እንደምታስቀምጠው ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡ ይሄ ባይተዋርነት ሆነ ተብሎ ከሚሰነዘር አግላይነት ጋር ሲደመር ሕጽናዊነት የሚለው ቃል ገቺ ወይም አግላይነት ይኖረዋል” (የአብሮነት ቃል)
በተጨማሪም… “አንድ ጽንሰ-ሐሳብ በትንሽ ነገር እንኳን ቢለይ አዲስ ስያሜ ማውጣት መብት አለኝ፡፡ ማንም አለው፡፡ ለምሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች በቅርፅ የራሳቸውን ባህርይ ልሰጣቸው እሞክራለሁ፡፡ አዲስ ጉዳይ ቅርፅ ነው፡፡ ለአስተማሪነት ቀበቶዬን አጥብቄ አላውቅም፤ የማን ወገብ ከማን ይበልጣል፡፡ የማንስ ድግ” (ግራጫ ቃጭሎች፤ እንደ መግቢያ)፡፡ ይሄ የአዳም አባባል ወጥ ሆኖ እስካሁን ቀጥሎ “ሕጽናዊነት ያሳያል እንጂ አይሰብክም” ይላል፡፡ (መረቅ፤ ገጽ 599) “ስራዬ በገለልተኛ ንቅናቄ መስታዎቱን የመገለባበጥ ነው፡፡ ተዳፋቱን እዚያ እና እዚህ በማድረግ ያለመጠን እውነታ ከፍርድ ሳይጠጉ ለአንባቢ ዐይን ማብቃት ነው፡፡” (“ግራጫ ቃጭሎች”፤ እንደ መግቢያ፡፡) ወይም ደግሞ በቀላሉ ለማስቀመጥ፡- “ሕጽናዊነት ያሳያል እንጂ አይሰብክም”፡፡ ሕጽናዊነትና ራይዞም (Rhyzome) “ጂኦሜትሪና ልቦለድ አፃፃፍ ያላቸው ግንኙነትና ትርጉም ስለሳበኝ ንባቤን በመጠኑ አሰፋሁና ይሄን በሚመለከት የተደረጉ ነገሮች እንዳሉ ለማጥናት ልሞክር ብል ከመጀመሪያ መጀመር ግድ ይላል፡፡ ከላይ እንዳልኩት ያለሁበት የግል ሁኔታ የተለየ ነው፡፡ ከጀርባዬ ሰፊ የድርሳን ትንታኔ፣ ረቂቅ የሂስና የፍልስፍና ባህል የለም፡፡ ያን አድካሚ ጉዞ ካላሳለፈ ህብረተሰብ ነው የወጣሁት፡፡ በግልም ደረጃ በሁሉም አቅጣጫ ሊያስኬደኝ የሚችል የፍልስፍና ዕውቀት ያጥረኛል፡፡ እኔ የመጣሁት ከጉዳዩ ጀርባ ነው፡፡ ይህ ማለት በመከወን ሂደት ውስጥ ካጋጠመኝ ጥቅንጥቅ እንጂ ከትወራ ጥናት አልተነሳሁም፡፡ ያለሁበትን ሁኔታ በቲዮሪ ለመረዳት ስሞክር ካደረግሁት ትንሽ ልፋት የተረዳሁት፣ [ሕጽናዊነት] ጓታሪና ደሉዝ፤ “ካፒታሊዝምና ስኪዞፌርኒያ” (Capitalism and Schizophrenia) በተባለው መጽሐፋቸው ከጠቀሱት ራይዞም [Rhizome] ከተባለው ሞዴላቸው (የማሕበረሰብና የዕውቀት ሞዴል) ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ነው፡፡ ራይዞምን የሀሳብ ምስል ነው ይሉታል፡፡ በተለይ የኢንተርኔት መምጣት የዚህን ፅንሰ ሀሳብ ቦታ ከፍ አድርጎታል፡፡ በብዙ በኩል ሕጽናዊነት ከዚህ የሚመሳሰል ሆኖ ሳለ፣ ራይዞም ተዋረድን (hierarchy) ቦታ ባለመስጠቱ የሚለይ ይሆናል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. ከዘጠናዎቹ መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ተፅዕኖ ማሳደር የጀመረው በይነ ዲሲፕሊናዊው ኢኮሎጂካል ትወራ የግንኙነትን ቸል መባል ፍቆታል፡፡ የሕጽናዊነት አንዱ አጀንዳ በመስመር ሳይሆን በመረብ ስልት የማሰብ ነው፡፡ ይሄ የሰለጠኑት በተባሉ አገሮች እንግዳ ላይሆን ይችላል፡፡ የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ መርቀቅና የመረጃ መረቦች መንሰራፋት እንግዳ አያደርጉትም፡፡ እንደኛ ባለ ቴክኖሎጂ ባልዳበረበት ሕብረተሰብ ውስጥ ይሄን ማንሳት ነገሩ ሳይመጣ ትንሽ መቅደም ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አካባቢ ለብዙ ሺህ ዘመናት የኖረ ነው፡፡ መረቡ ትራንስፖርትና ኤሌክትሮኒክስ ባይሆንም ጀነቲክ፣ ቋንቋ፣ ጦርነትና የንግድ ግንኙነት ነው”፡፡ (የአብሮነት ቃል) ከሕጽናዊነት ባሻገር፡ ጠጠር መጣልና ብዕር መጣል በ”እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ውስጥ የሚገኘው መስኮት ገረሱ የተባለ ሰዓሊ የስዕል ሥራዎቹ ከየትና እንዴት እንደመጡ (እንዴት ሊፈጥራቸው እንደቻለ ባለማወቁ) ስዕል መሳልን ከጠጠር ጣይነት ጋር ያወዳድረዋል፡፡ “ስዕል መሳል ከጠጠር መጣል ጥንቆላ ጋር ስለሚመሳሰልብኝ ነው፡፡ አንዳንድ ኪነታዊ ውጤቶቼን ሳይ በአብዛኛው ሳላስባቸው የመጡ ናቸው፡፡ ከየት መጡ? ማን መራኝ? እነዚህ ጥያቄዎች ያገሬን ጠንቋይ ያስታውሱኛል፤ የኪነት የፈጠራ ሂደትን የአስማታዊነት ፈርጅ አያለሁ፡፡ ከየት እንደመጡ ካላወቅሁ ከጠጠር ጣይና ከኮከብ ቆጣሪ ምን ይለየኛል?” (ገጽ 43 - 44)፡፡ እኛስ “ጠጠር መጣል” ተብሎ “ብሩሽ መጣል” ከተባለ “ብዕር መጣል” ማለት እንችል ይሆን? የአዳም ማብራሪያ ለዚህ ይሁኝታ የሚሰጥ ይመስላል፡፡ “አለንጋና ምስር” በተባለው መጽሐፉ ውስጥ የሚገኘውን “ዘላን” የተሰኘ ትረካ በጠልሰም መልኩ ለማስቀመጥ እንደሚቻል ሲያብራራ፤ “እንዲህ ስናደርግ [ጠልሰም ስንሠራ] ያልታቀዱ/ያልተገመቱ ግንኙነቶችን ነው የምንስለው፡፡ የሚመጣው ውጤትም ቀድሞ የታቀደ አይደለም”፡፡ There are of course stochastic processes involved in this. Outcomes are not a priorily designed ይላል አዳም፡፡ አዳም ይሄንን ያለው ለሁሉም ልቦለዶቹ ነው ብለን ብንለጥጠው ታዲያ ድርሰት መጻፍ ብሩሽ መጣል አልሆነም? መስኮት ከ”ጠጠር መጣል” ወደ “ብሩሽ መጣል” ከሄደ እኛስ አዳምን ወደ “ብዕር መጣል” ብንወስደው ምን ይለናል? አዳምም ያለነገር አይደለም ስለ “ጠልሰም” እና “ክታብ” ብዙ የሚያብራራው ብንልስ ያስኬደናል? አዳም ስለ ሕጽናዊነት ሲያብራራ በተደጋጋሚ የሚጠቅሳቸው ሁለት ቃላት አሉ፡፡ እነኚህን ቃላት በተለምዶ የምናውቃቸው ከአስማት፣ ከድግምትና ከመሳሰለው ነገር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እነኚህ ቃላት “ጠልሰም” እና “ክታብ” ናቸው፡፡ ትርጓሜያቸውን አስቀምጠን እንቀጥል፡- ጠልሰም፡- የተለያየ ስዕል ያለበት የጥንቆላና የአስማት ጽሑፍ የያዘ ጥቅል ብራና ወይም ወረቀት፡፡ (አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ማዕከል፤ 2001 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ) ክታብ፡ ከበሽታ እንዲያድን ወይም ከክፉ ነገር እንዲጠብቅ ተብሎ በብራና ወይም በወረቀት ላይ ተፅፎና ተጠቅልሎ በአንገት ወይም በክንድ ላይ የሚታሰር መድኃኒት፡፡ (ዝኒ ከማሁ) እነኚህ ከላይ ከመዝገበ ቃላት ፍቻቸው ጋር የተቀመጡት ሁለት ቃላት ከአዳም ድርሰት በተለይም ከሕጽናዊነት ጋር ምን አገናኛቸው? በወረቀትና በብራና ላይ ተስሎ ከበሽታና ከክፉ ነገር እንዲያድን በክንድ ወይ በአንገት ላይ የሚንጠለጠለው ጠልሰም ወይም ክታብ ውስጡ ተፈትቶ ቢታይ ሌላ ተዓምር የለውም፡፡ መረባዊ ግንኙነት ያላቸው መስመሮችን የሚያሳይ ስዕል እንጂ፡፡ “ጠልሰም ማለት መረባዊ ግንኙነት ነው፤ ሕጽናዊነትም ያለ ጥርጥር እንደዚያው” … Telsem is all about interconnectivity which hitsinawinet undoubtedly is. ታዲያ በታሪኮቹ ውስጥ ጠልሰምን መሥራት ብቻ ሳይሆን በአንገታችን እንድናንጠለጥል የሚጋብዘው ይሄ “ምትሃተኛ” ደራሲ፤ “…ይሄም ማለት በአጋጣሚ የጠፉ ወይ ደግሞ ሆነ ተብለው እንዲጠፉ የተደረጉ የግንኙነት መረቦችን ፍለጋ መውጣት ነው ይላል”፡፡ …meditate on the injera. Carry an injera Telsem around your neck……in your mouth. This means look for connections, arbitrarily lost or purposely subdued. በቅርቡ የወጣው “መረቅ” የተሰኘ መጽሐፉ በፊት ሽፋኑ “ሞዴል ጠልሰም” ይዞ ከመውጣቱ በፊት ደግሞ አዳም ይሄን ብሏል… “ለወደፊት ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ውስብስብ የሆኑ ልቦለዶችንና ታሪኮችን ባለ ሁለትና ባለሦስት ዲሜንሽናል ጠልሰሞችን በማዘጋጀት ከልቦለድነትም ባሻገር እንደሚታዩ የጥበብ ውጤቶች (visual art products) ወስደን ልናነፃፅራቸው (ልናደንቃቸውም) እንችል ይሆናል”.” ደራሲው ቀድሞ እንዳለውም “መረቅ” ላይ ጠልሰሙን ከነ”የአሠራር ቅደም ተከተል መመሪያ”ው ይዞ መጣ፡፡ በዚህ መጽሐፍ መውጫ የመጽሐፉ ትዕምርት መሆን የሚችለው ጠልሰም እንዴት እንደሚሠራ ሲያብራራ በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጾች ላይ ማየት ይቻላል፡፡ የሽፋን ስዕሉ ላይ ያለውን ጠልሰም ሲያብራራ… ”ደራሲው ይሄን ጠልሰም ለመስሪያ የተጠቀመባቸው ቃላቶች አንጓ፣ መለልታና መረቅ የተባሉትን ብቻ ነው፡፡ ስዕሉ ‘መረቅ’ የተባለው ይሄን ልቦለድ ‘ወካይ’ ነው” ብሏል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ሕጽናዊነት እስከዛሬ ከለመድናቸው የተለዩ የሂስ ስራዎችን እንድናዳብር ይገፋፋናል፡፡ በቋንቋ ብቻ ከማጥናት በምስልና በአሃዝ ማጥናትና መተቸት ያስችለናል፡፡ ለምሳሌ በመረብ ካርታ (network mapping) ወይም በአክተር ኔትወርክ ቲዮሪ ቋንቋ ውስብስብ ካርታዎች (complexity mapping) በመስራት፣ ወይም በዲስኮርስ አናሊሲስ ካርታ (discourse analysis mapping) አልፎ ተርፎም በአሃዝ ማስላት እንድንችል ይገፋፋናል፡፡ ከቃላት ዘልቆ የገጸባሕሪያት ቦታ (space) በነዚህ ዓይነት ውስብስብ ጠልሰሞች ሊታይ፣ ሊገለጽና ሊገመገም ይችላል፡፡ በመጨረሻም እንጀራውን እንብላው… እንጀራ ሊበላ የሚችል/በምግብ መልኩ የቀረበ/ ብራና ነው … “It is an edible Brana” እንዲል ደራሲው፡፡ እንግዲህ ደራሲው አዳም ረታ ከዚህ በፊት በነበሩት መጻሕፍቱ እንጀራው እንዴት እንደሚሠራ ከሚለው ጀምሮ የመጋገር ሂደቱን፤ አቀራረቡን፤ የተመጋቢዎችን አሰላለፍ፤ ጉርሻውን፤ የጉርሻ አሠራርና ይዘቱን ወዘተ ሲያስረዳን ቆይቶ በስምንተኛው መጽሐፉ መረቅ ደግሞ እንድንበላው አቅርቦልናል፡፡ “የሴራ ሂደት/ ምት/ የቃላት አሰዳደር ወዘተ ለእኔ ወጡ በእንጀራው ላይ ከሚያደርገው ፍሰት ጋር ይመሳሰላሉ፤ ልክ ውሀ በስፖንጅ ውስጥ ወይም ደግሞ በአፈር ውስጥ ሰርጎ ሲገባ ዓይነት” የሚለው አዳም፤ “የማንበብ ሂደቱ እንጀራውን መዘርጋት፣ እንጀራው ላይ ወጥ/መረቅ የማፍሰስ፣ በሂደቱም መጎራረስ፣ በስተመጨረሻም የቀረውን አንድ ገጽ የመረቅ ቅሬት ጠርጎ መብላትን ያካትታል፡፡ ‘የመጽሐፍ ቀበኛ’ አለነገር አላሉም አበው” ይላል በገጽ 600፡፡
Comments